1
ፈሪሳውያን ከዮሐንስ ይልቅ ኢየሱስ ብዙ ደቀ መዛሙርትን እንዳፈራና እንዳጠመቀ ሰሙ፤
2
ዳሩ ግን ያጠመቀው ኢየሱስ ሳይሆን ደቀ መዛሙርቱ ነበሩ።
3
ጌታም ይህን እንዳወቀ ይሁዳን ለቆ ወደ ገሊላ ተመልሶ ሄደ።
4
በሰማርያም በኩል ማለፍ ነበረበት።
5
ስለዚህ በሰማርያ፣ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ወደ ነበረች፣ ሲካር ወደምትባል ከተማ መጣ።
6
በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጒድጓድ ነበረ፤ ኢየሱስም ከጒዞው የተነሣ ደክሞት ስለ ነበር በውሃው ጒድጓድ
አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ነበር።
7
አንዲት ሳምራዊት ሴት ውሃ ለመቅዳት ስትመጣ ኢየሱስ፣
“እባክሽ የምጠጣው ስጪኝ”
አላት፤
8
ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ለመግዛት ወደ ከተማ ሄደው ነበር።
9
ሳምራዊቷም፣ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ፣ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት ውሃ አጠጪኝ ትላለህ?” አለችው፤ ይህን
ማለቷ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር ስለማይተባበሩ ነው።
10
ኢየሱስም፣
“የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ፣ አንቺው በጠየቅሽው፣
እርሱም የሕይወትን ውሃ በሰጠሽ ነበር”
ሲል መለሰላት።
11
ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ መቅጃ የለህም፤ ጒድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ ይህን የሕይወት ውሃ
ከየት ታገኛለህ?
12
ለመሆኑ አንተ፣ ይህን ጒድጓድ ከሰጠን፣ ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱ ራሱና ልጆቹ፣ እንስሳቱም
ከዚሁ ጒድጓድ ጠጥተዋል።”
13
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላት፤
“ከዚህ ውሃ የሚጠጣ እንደ ገና ይጠማል፤
14
እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት
ውሃ ምንጭ ይሆናል።”
15
ሴትዮዋም፣ “ጌታዬ፤ እንዳልጠማና ውሃ ለመቅዳት እንዳልመላለስ፣ እባክህ ይህን ውሃ ስጠኝ” አለችው።
16
እርሱም፣
“ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ተመለሽ”
አላት።
17
ሴትዮዋም፣ “ባል የለኝም” ብላ መለሰች።
ኢየሱስም፣ እንዲህ አላት፤
“ባል የለኝም ማለትሽ ትክክል ነው፤
18
በርግጥ አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁን ከአንቺ ጋር ያለውም ባልሽ ስላልሆነ፣ የተናገርሽው እውነት
ነው።”
19
ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ አንተ ነቢይ እንደሆንህ አያለሁ፤
20
አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፤ እናንተ አይሁድ ግን ሰው መስገድ ያለበት በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ”
አለችው።
21
ኢየሱስም እንዲህ አላት፤
“አንቺ ሴት፤ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ እንደሚመጣ እመኚኝ።
22
እናንተ ሳምራውያን ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ግን ድነት ከአይሁድ ስለ ሆነ ለምናውቀው
እንሰግዳለን።
23
በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቶአል፤ አብም
እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል።
24
እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።”
25
ሴትዮዋም፣ “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ነገር ይነግረናል” አለችው።
26
ኢየሱስም፣
“የማነጋግርሽ እኮ እኔ እርሱ ነኝ”
ሲል ገልጦ ነገራት።
ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው መጡ
27
በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው መጡ፤ ከሴት ጋር ሲነጋገር በማግኘታቸው ተደነቁ፤ ሆኖም ግን፤ “ምን
ፈለግህ?” ወይም፣ “ከእርሷ ጋር የምትነጋገረው ለምንድን ነው?” ብሎ የጠየቀው ማንም አልነበረም።
28
ሴትዮዋም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ተመለሰች፤ ለሕዝቡም፣
29
“ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እርሱ ክርስቶስ
ይሆን እንዴ?” አለች፤
30
እነርሱም ከከተማ ወጥተው እርሱ ወዳለበት አመሩ።
31
በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፣ “ረቢ፣ እህል ቅመስ እንጂ” አሉት።
32
እርሱ ግን፣
“እናንተ የማታውቁት፣ የምበላው ምግብ አለኝ”
አላቸው።
33
ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሰው ምግብ አምጥቶለት ይሆን እንዴ?” ተባባሉ።
34
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤
“የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው፤
35
እናንተ፣ ‘ከአራት ወር በኋላ መከር ይደርሳል’ ትሉ የለምን? እነሆ፣ አዝመራው ለመከር እንደ ደረሰ
ቀና ብላችሁ ማሳውን ተመልከቱ እላችኋለሁ።
36
አጫጁ አሁንም ቢሆን እንኳ ደመወዙን እየተቀበለ ነው፤ ለዘላለም ሕይወት ይሆን ዘንድ አዝመራውን
ይሰበስባል፤ ይህም ዘሪውና አጫጁ በጋራ ደስ እንዲላቸው ነው።
37
ስለዚህ፣ ‘አንዱ ይዘራል፤ ሌላውም ያጭዳል’ የተባለው ምሳሌ እውነት ነው።
38
ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ አድካሚውን ሥራ ሌሎች ሠሩ፤ እናንተም የድካማቸውን ፍሬ
ሰበሰባችሁ።”
ብዙ ሳምራውያን አመኑ
39
ሴትዮዋ፣ “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ” ብላ ስለ መሰከረች፣ ከዚያች ከተማ ብዙ ሳምራውያን በእርሱ አመኑ።
40
ስለዚህ፣ ሳምራውያኑ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ አብሮአቸው እንዲቈይ አጥብቀው ለመኑት፤ እዚያም ሁለት ቀን
ቈየ።
41
ከቃሉም የተነሣ ሌሎች ብዙዎች አመኑ።
42
ሴትዮዋንም፣ “ከእንግዲህ የምናምነው አንቺ ስለ ነገርሽን ብቻ አይደለም፤ እኛ ራሳችን ሰምተነዋል፤ ይህ
ሰው በእውነት የዓለም አዳኝ እንደሆነ እናውቃለን” አሏት።
ኢየሱስ የሹሙን ልጅ ፈወሰ