ትንቢተ ኢሳይያስ 52:13-53:12
13 እነሆ፥ ባሪያዬ በማስተዋል ያደርጋል፤ ይከብራል ከፍ ከፍም ይላል፥ እጅግ ታላቅም ይሆናል።
14 ፊቱ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ፥ መልኩም ከሰዎች ልጆች ይልቅ ተጐሳቍሎአልና ብዙ ሰዎች ስለ አንተ እንደ ተደነቁ፥ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን ያስደንቃል፤
15 ያልተነገረላቸውንም ያያሉና፥ ያልሰሙትንም ያስተውላሉና ነገሥታት ስለ እርሱ አፋቸውን ይዘጋሉ።
53:1 የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል?
2 በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል፤ መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም።
3 የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም።
4 በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።
5 እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።
6 እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።
7 ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
8 በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ?
9 ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ፤ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር።
10 እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።
11 ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሸከማል።
12 ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።
የዮሐንስ ወንጌል 1:29-34
29 በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።
30 አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።
31 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ።
32 ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ፦ መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ።
33 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፦ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ።
34 እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።
የኢሳይያስ 52:13-53:12 መግቢያ
ባለፈው ግዜ እግዝአብሔር አዲስ ዘመን እንደሚመጣ ማሳወቁን አምብበናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ይህ እንዴት እንዴት እንደ ተፈጸመ እናያለን፡፡ እግዝአብሔር “ባርያውን” ይልካል፡፡ ያም እግዝአብሔር እንዳሰበው በትክክል የሚኖር ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ከኃጥአት ሳይኖረው እንደ ወንጀለኛ ይሞታል፡፡ ምክንያቱም የዚህ የእግዝአብሔር ባርያ ተልዕኮ የሰውን ልጅ ድካም፣ ሕመም፣ ስቃይና ኃጥአት በራሱ ላይ መሸከም ይሆናል፡፡ ይህም ጥሩ ራዕይ አይመስልም፤ ፈጽሞ ተቃራኒ ነው፡፡
ነገር ግን በዙሪያው ያሉት ሰዎች ከርሱ ዞሩ እንጂ አልተቀበሉትም፡፡ ነገር ግን በሰራው ወንጀል በእግዝአብሔር እንደ ተቀጣ ወንበዴ ወይም ወንጀለኛ ቆጠሩት፡፡ እውነቱ ግን በራሱ ክፉ ስራ የተቀጣ አልነበረም፤ በክፋት ተፅዕኖ ስር ያሉት ሰዎች በሰሩት ክፋት ነበር እንጂ፡፡ ይህ የእግዝአብሔር ባርያ ለክፉ ስራችን ኃላፍነት ይቀበላል፡፡ በኛ በኃጥአተኞች ፋንታ ይከሰሳል፤ ይሰቃያል፡፡ ይህም እኛ ተመልሰን ሰላም እንድናገኝ፤ ከእርስበርሳቻን እና ከእግዝአብሔር ጋር ሰላም እንዲኖረን ነወ፡፡
ዮሓንስ (መጥምቁ) ለሚመጣው የእግዝአብሔር ባርያ መንገድ ለማዘጋጀት ከእግዝአብሔር የተላከ ነብይ ነበረ (ኢሳይያስ 52-53)፡፡ በዚህ ንባብ ውስጥ ኢየሱስ የአለምን ኃጥአት የሚሸከም የእግዝአብሔር በግ እንደ ሆነ ገለጦ መሰከረለት፤ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ በክፋት ስር የነበረውን የሰው ማንነት ልያድን ለመጣ ያለው ነው ማለቱ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ የሰውን ኃጥአት እና ቅጣቱን በራሱ ላይ በመውሰድ ነው፡፡
![]() |
![]() |
![]() |